የኤች አይቪ ምርመራ በካናዳ

የኤች አይቪ ምርመራ

 

የኤች አይቪ ምርመራን ማድረግ ለምን ያስፈልጋል?

በካናዳ ውስጥ ከኤች አይቪ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ 25% ያህሉ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ አያውቁም። ነገር ግን የኤች አይቪ ቫይረስ ምርመራን በጊዜ አድርጎ እራስን ማወቅ የሚከተሉትን ጠቀሜታዎች ያስገኛል።

 • የስጋት ስሜትን ያስወግዳል፥
 • ውጤቱ ከቫይረሱ ነፃ ቢሆንም በምርመራ ወቅት በጤና ባለሙያ የሚሰጥ መረጃ ለወደፊት እራስን በምን አይነት መልኩ ከቫይረሱ መጠበቅ እንደሚቻል ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የማግኘት እድል ይከፍታል፥
 • ቫይረሱ በደም ውስጥ ካለ ፥ ተገቢ የምክር አገልግሎት፥ እንክብካቤ እና የሕክምና አገልግሎት እንዴት ማግኝት እንደሚቻል ግንዛቤ የማስጨበጥ እድል ይሰጣል። በተጨማሪም በተደጋጋሚ ለቫይረሱ መጋለጥ (re-infection) ክስተት እንዳይኖር ጥንቃቄ የማድረግ እድልን ይሰጣል። ቫይረሱ ስውነትን ሳያጠቃ በጊዜ በደም ውስጥ መኖሩ ከታወቀ የሕይወት ማራዘሚያ መድሃኒቶችን በተገቢው ወቅት ለመጀመር እንዲቻል እንዲሁም የቫይረሱ ወደሌሎች የመተላለፍ ሁኔታ እንዲቀንስ ይረዳል።

 

የኤች አይቪ ምርመራ ማድረግ ያለባቸው እነማን ናችው?

 • ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግኑኝነት ያደረጉ እና ተመርምረው የማያውቁ፥
 • ከሰውነት የጤና መከላከል( immune system) ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና ጉድለት (Infection) ያጋጠማቸው፥
 • ለአደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያነት የሚያገለግሉ መርፊዎችን የተጋሩ፥
 • እርጉዝ ሴቶች፥ ወይንም እንደየአስፈላጊነቱ ለማርገዝ አላማ ያላቸው ጥንዶች እና በእርግዝና ወቅት ለኤች አይቪ የተጋለጡ፥
 • የፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ፥ እና
 • የአባለዘር በሽታዎች ፥ Hepatitis B, C ፥ የሳንባ ነቀርሳ እና ሌሎች በብዛት ከኤች አይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎች (infection) የገጠማቸው በዋነኛነት የኤች አይቪን ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።

 

የኤች አይቪ ምርመራን የት ማድረግ ይቻላል?

የኤች አይቪ ምርመራን በየትኛውም የጤና ማእከል ሥር ወይም መሪነት (referral) ማድረግ ይቻላል። በቶሮንቶ ውስጥ ብዙ የግበረ ስጋ ጤና ጣቢያዎች (Sexual Health Clinics) የኤች አይቪ ምርመራ አገልግሎትን ይሰጣሉ። አብዛኞቹ እነዚህ ጣቢያዎች የሐኪም ማዘዣ (referral) ወይንም የነፃ ሕክምና ካርድ (OHIP) የሌላቸውንም ተቀብለው ያስተናግዳሉ።

 

በካናዳ ውስጥ የሚገኙ የኤች አይቪ ምርመራ አማራጮች

 • ስም አስመዝግቦ የሚደረግ ምርመራ ( Nominal HIV testing)

የጤና ማእከሉ የተመርማሪውን/ዋን ስም እና ሌሎች መለያ መረጃዎችን በማያያዝ ለናሙና የተወሰደውን ደም ለቤተ ሙከራ ይልካል። የጤና ማእከሉ በተመርማሪው/ዋ ደም ውስጥ ኤች አይቪ ከተገኝ እንደ አስፈላጊነቱ ውጤቱን እስክ እነ ተመርማሪው/ዋ ስም እና ሌላ መለያ መረጃ ጋር ለጤና ጥበቃ ቢሮ እንዲያስተላልፍ በሕግ ይገደዳል።

 • ስም ሳይሰጥ የሚደረግ ምርመራ (Non – Nominal testing)

የምርመራ ሂደቱ ከላይ ስም አስመዝግቦ እንደሚደረግ የምርመራ አይነት ሆኖ ልዩነቱ የጤና ማእከሉ በተመርማሪው/ዋ ስም ፈንታ መለያ ኮድ በመመዝገብ የደም ናሙናውን ለቤተ ሙከራው ( laboratory) ያስተላልፋል። እንደ አስፈላጊነቱ በተመርማሪው/ዋ ደም ውስጥ ቫይረሱ ከተገኝ ውጤቱ እስከ እነ ተመርማሪው/ዋ ስም እና መለያ መረጃ ለጤና ጥበቃ ይተላለፋል።

 • ማንነት ሳይገለፅ የሚደረግ ምርመራ (Anonyms HIV testing)

የጤና ማእከሉ የተመርማሪውን/ዋን ማንነት የሚገልፅ ማንኛውንም መረጃ አይመዘግብም። ባንዳንድ ቦታዎች የምርመራ ውጤቶች ለጤና ጥበቃ መላክ ሊኖርበት ይችላል። ነገር ግን የተመርማሪዎቹን ማንነት የሚገልፅ መረጃ ሳይሆን በደፈናው የኤች አይቪ ስርጭት ሁኔታን ለማወቅ የሚረዳ መረጃ ይሆናል።

 

የኤች አይቪ ምርመራ ሂደት አይነቶች

የኤች ኣይቪ ምርመራን ላማድረግ እንደ ምርመራው አይነት ከተመርማሪው/ዋ ጣት ወይንም ደም ሥር ደም ይወስዳል። በካናዳ ውስጥ የሚከተሉት የኤች አይቪ ምርመራ ሂደት አይነቶች ይገኛሉ፥

 • መደበኛ ምርመራ (Standard HIV testing)

አብዛኞች ሆስፒታሎች ፥ የቤተሰብ ሃኪሞች እና የጤና ማእከላት መደበኛ (Standard) የኤች አይቪ ምርመራን ያደርጋሉ። በዚህ የምርመራ አይነት ደም በ (tube) ከደም ስር ይወስድና ወደ ቤተ ሙከራ ይላካል። ውጤቱም በአብዛኛው ጊዜ በሳምንት ውስጥ ይደርሳል።

 • ፈጣን ምርመራ ( Point- of – care or rapid testing)

የዚህ አይነቱ የኤች አይቪ ምርመራ ውጤት በአንድ የጤና ማእከል ጉብኝት የሚጠናቀቅ ነው። የኤች አይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ ካልተገኘ እና ተመርማሪው/ዋ ከምረመራው በፊት ባሉ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለቫይርሱ የመጋለጥ እድል ካልነበረው/ራት ከምርመራ በኃላ የሚሰጥ የምክር አገልግሎት ተቀብሎ/ላ ከቫይረስ ነፃ መሆኑን ተረድቶ/ታ ይሄዳል/ለች። ተመርማሪው/ዋ ከምርመራው ቀደም ብሎ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ ለቫይረሱ የመጋለጥ ሁኔታ ኖሮታል/ቷል ተብሎ ከተገመተ መደበኛ ምርመራ እንዲደረግ የደም ናሙና ወደ ቤተ ሙከራ ይላካል። እንዲሁም ተመርማሪው/ዋ ውጤቱን ለመቀበል በሌላ ቀን እንዲመለስ/እንድትመለስ ይደረጋል። በፈጣን ምርመራ ቫይረሱ በደም ውስጥ እንዳለ ከታየም እርግጠኛ ለመሆን እንደገና መደበኛ ምርመራ እንዲደረግ ይደረጋል።

የኤች አይቪ ቫይረስ በደም ውስጥ ከተገኝ ተመርማሪው/ዋ ከጤና ባለሙያው ጋር በቀጣይነት መደረግ ስላለበት እርምጃ ውይይት ያደረጋል/ታደርጋለች። የጤና ባለሙያው፥ ተመረማሪው/ዋ መቼ መድኅኒት መጀመር እንዳለበት/ባት እና የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ሰዎች የተለያየ ድጋፍ በመስጠት ላይ ስለሚገኙ ተቋሞች መረጃዎችን ይሰጣል።

* በካናዳ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በካናዳ ጤና ጥበቃ ፈቃድ ያገኝ ለቤት ውስጥ የኤች አይቪ መመርመሪያነት የሚያገለግል መመርመሪያ (Testing Kit) የለም።

 

የበለጠ መረጃ ካሻዎት ወደ AIDS and Sexual Health Info line at 416-392-2437 or Toll Free at 1 800 668-2437 ውይንም ወደ ኢትዮጲያ ማህበር 416 694 1522 ext. 27/58 በመደወል ማግኝት ይችላሉ።